FAQ Page

የጤና መድህን ማለት ለተመሳሳይ የጤና ችግር የተጋለጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ግለሠቦችና ቤተሠቦች በጋራ በማሠባሠብ እያንዳንዱ ግለሠብ ወይም ቤተሰብ የሚደርስበትን የጤና ወጪ በጋራ በተቋቋመው የጤና ፈንድ አማካኝነት በመሸፈን ለግለሠቦች ወይም ቤተሠቦች ያልታሰቡ ከፍተኛ የጤና ወጪዎችን ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት የሚረዳ ስልት ነው፡፡( የዓለም የስራ ድርጅት)

እያንዳንዱ ግለሠብ ወይም ቤተሠብ በህይወት ውስጥ የጤና እክል መቸ እና እንዴት ሊያጋጥመው እንደሚችል መተንበይ ስለሚያዳግተው በጤና መድህን ስርዓት በመታቀፍ እነዚህን ስጋቶች ማስወገድ ይችላል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ለመተንበይ አስቸጋሪ የሚሆነው የጤና ስጋትና እና የወጪ መጠን በጋራ በሚሆንበት ጊዜ ለመተንበይ በአንፃራዊነት ስለሚቀል ለጤና የሚያስፈልገውን የመዋጮ መጠን በቀላሉ መወሰን ይቻላል፡፡

የጤና መድህን ስርዓት አሠራር ግለሠቦች ወይም ቤተሠቦች ወደፊት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ብሎም ቀውስ ወደ አስቀድሞ የሚደረግ አነስተኛ እና የታወቀ የጤና መዋጮ ስለሚቀይረው ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በአጠቃላይ በጤና መድህን አሠራር ዜጎች ጤናማ በሚሆኑበት ወቅት በሚከፍሉት አነስተኛ መዋጮ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት ከመድህን ቋቱ ወጪ በሚደረግ ገንዘብ የጤና ወጪአቸው ይሸፈንላቸዋል፡፡

ይህ ሥርዓት በመደበኛው ክፍለ ኢኮኖሚ ተሰማርቶ የሚገኘውን/ደመወዝተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያቅፍ ሲሆን የአሠራር የህግ ማዕቀፍ ወጥቶለት ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡

ይህ ሥርዓት መደበኛ ባልሆነ ገቢ የሚተዳደሩትን ወይንም ደመወዝተኛ ያልሆኑ  በገጠርና በከተማ የሚገኙ ዜጎችን የሚያቅፍ የመድህን ሥርዓት ነው፡፡ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በ2003 ዓ.ም በአራቱ ክልሎች (ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች) ባሉ 13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ ፤ ከእነዚሁ ወረዳዎች የተገኘውን መልካም ልምድ በመገምገም ሙከራውን ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለማስፋት በተደረገው ጥረት ፕሮግራሙ የሚተገበርባቸው ወረዳዎች ቁጥር ከ365 በላይ ደርሷል፡፡

የሚከተሉትን የጤና አገልግሎቶች ተጠቃሚ ናቸው፡

  • የተመላላሽ ሕክምና፣
  • የተኝቶ ሕክምና፣
  • የወሊድ አገልግሎት፣
  • የቀዶ ህክምና፣
  • በሕክምና ባለሙያዎች የታዘዙ የምርመራ አገልግሎቶች እና መድሀኒቶች ይገኙበታል፡፡

 

 የተመላላሽ ህክምና (Outpatient)

የተመላላሽ ህክምና ሲባል ህሙማን በማንኛውም ደረጃ ባለ የጤና ተቋም ተኝተው መታከም ሳያስፈልጋቸው በተመላላሽ ደረጃ የህክምና ባለሙያዎችን እያገኙ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ነው፡፡

በዚህ አገልግሎት ሥር ለጤና መድህን አባላትና ቤተሰቦች የሚሠጡ ዋና ዋና የህክምና አገልግሎቶች፡-

· የካንሰር ህክምና (Cancer)፣

· የደም ግፊት ህክምና (Hypertension)፣

· የስኳር ህክምና (Diabetes)፣

· የልብ ህክምና፣

· የወሊድ አገልግሎት፣

· የህጻናት ህክምና፣

· የውስጥ ደዌ ህክምና፣

· የአእምሮ ህክምና፣

· የቀዶ ጥገና ህክምና (Surgical Service)፣

· የአጥንት ህክምና (Orthopedics)፣

· ከአንገት በላይ ህክምና (ENT)

· የዓይን ህክምና  (Ophthalmology)፣

· የጥርስ ህክምና (Dental)፣

· የላብራቶሪ ምርመራ፣ (Laboratory)

· የራጅ ምርመራ አገልግሎት (X-Ray)፣

· የፊዝዮቴራፒ ህክምና (Physiotherapy)፣

· የፕሮሲጀር ምርመራ አገልግሎት (Diagnostic Procedures) እና

· ሌሎች በተመላላሽ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን ማግኘት ይቻላል፡፡

2  የተኝቶ ህክምና (Inpatient)

የተኝቶ ህክምና ሲባል ህሙማን ያጋጠማቸው የህመም ደረጃ በጤና ተቋም ተኝቶ/አልጋ በመያዝ በህክምና ባለሙያዎች ቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው  የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ሥር የሚከተሉት ህክምናዎች ለጤና መድህን አባላትና ቤተሰቦች ይሰጣሉ፡፡

· የሄፓታይተስ ህክምና (Hepatitis)፣

· የደም ግፊት ህክምና (Hypertension)፣

· የልብ ህክምና (Cardiac Vascular diseases)፣

· የፅኑ ህሙማን ክትትል (Intensive Care)፣

· ቀዶ ጥገና ህክምና (Surgery)

· የካንሰር ህክምና (Cancer)፣

· የስኳር ህክምና (Diabetes)፣

· የአጥንት ስብራት ጥገና ህክምና (Fractures)፣

· የዓይን ህክምና (Ophthalmology)፣

· የውስጥ ደዌ ቴራፒ (Internal Medicine Therapy)፣

· የተቅማጥ ህክምና (ለአዋቂዎች) Diarrhea Infections)፣

· የጽንስና ማህጸን ህክምና (Gynecology)፣

· የጨቅላ ህጻናት ህክምና (Neonatal)፣

· የወሊድ አግልግሎት (Maternity)፣

· የአዕምሮ ህክምና (Mental health)፣

· የጥርስ ህክምና (Dental)፣

· የህጻናት ህክምና (Pediatric)፣

· የአንገት በላይ ህክምና (ENT) እና

· ሌሎች በተኝቶ ህክምና የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን ማግኘት ይቻላል፡፡

3. የቀዶ ጥገና ህክምና (Surgery)

· ቀላል ቀዶ ህክምና፣

· ከፍተኛ ቀዶ ህክምናና፣

· ስፔሻላይዝድ ቀዶ ህክምና ለምሳሌ፡- የልብ፣ የነርቭ፣ የአንጎል ቀዶ ህክምናና ሌሎች አገልግሎቶችን ያካትታል፡፡

4. የላቦራቶሪ አገልግሎት (Laboratory Investigation & Diagnostic Services)

ማንኛውም የጤና መድህን አባልና ተጠቃሚ በርካታ የላቦራቶሪ ምርመራና ዲያግኖስቲክ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላል፡፡ ለአብነትም የኤምአርአይ (MRI)፣

የሲቲ ስካን (CT-Scan)፣ የኢኮካርዲዮግራፊ

 (Echocardiography)፣ኢንዶስኮፒ Endoscopy)፣አልትራሳውንድ Ultrasound)፣

የኤክስሬይ (X-Ray)፣ልዩ ልዩ የኬሚስትሪ ምርመራዎች፣ ወዘተ…. ይገኙበታል፡፡ 

  5. የመድሀኒት አገልግሎት

የጤና መድህን አባልና ተጠቃሚ ወደ ሀገራችን እንዲገቡ የተፈቀዱ ማንኛውም ዓይነት መድሀኒቶችን የማግኘት መብት አለው፡፡ የመድሀኒቶቹ ዝርዝር ሰፊ በመሆኑ በዚህ አጭር መግለጫ ማስፈር ባይቻልም ከላይ ለተጠቀሱት የህክምና ዓይነቶች እና ሌሎችም ያልተዘረዘሩ በርካታ የህክምና አገልግሎቶች እንዲውሉ የተመረጡ 538 የመድሃኒት ዓይነቶች በጥቅም ማዕቀፉ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ ስለሆነ በኤጀንሲው ዋና መስሪያ ቤት ወይንም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ቀርቦ ሙሉ ዝርዝሩን መመልከት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ በሀገራችን የሚተገበረው የጤና መድህን ለአባላትና ቤተሰቦች እንዲሰጡ የሚፈቅዳቸው የጤና አገልግሎት ዓይነቶች ከአንዳንድ ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም ሰፊ እንደሆነ  ልብ ይበሉ፡፡