አጠቃላይ ገጽታ
አጠቃላይ ገጽታ
የጤና መድህን ምንድን ነው??
የጤና መድህን ማለት ለተመሳሳይ የጤና ችግር የተጋለጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ግለሠቦችና ቤተሠቦች በጋራ በማሠባሠብ እያንዳንዱ ግለሠብ ወይም ቤተሰብ የሚደርስበትን የጤና ወጪ በጋራ በተቋቋመው የጤና ፈንድ አማካኝነት በመሸፈን ለግለሠቦች ወይም ቤተሠቦች ያልታሰቡ ከፍተኛ የጤና ወጪዎችን ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት የሚረዳ ስልት ነው፡፡( የዓለም የስራ ድርጅት)
እያንዳንዱ ግለሠብ ወይም ቤተሠብ በህይወት ውስጥ የጤና እክል መቸ እና እንዴት ሊያጋጥመው እንደሚችል መተንበይ ስለሚያዳግተው በጤና መድህን ስርዓት በመታቀፍ እነዚህን ስጋቶች ማስወገድ ይችላል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ለመተንበይ አስቸጋሪ የሚሆነው የጤና ስጋትና እና የወጪ መጠን በጋራ በሚሆንበት ጊዜ ለመተንበይ በአንፃራዊነት ስለሚቀል ለጤና የሚያስፈልገውን የመዋጮ መጠን በቀላሉ መወሰን ይቻላል፡፡
የጤና መድህን ስርዓት አሠራር ግለሠቦች ወይም ቤተሠቦች ወደፊት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ብሎም ቀውስ ወደ አስቀድሞ የሚደረግ አነስተኛ እና የታወቀ የጤና መዋጮ ስለሚቀይረው ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በአጠቃላይ በጤና መድህን አሠራር ዜጎች ጤናማ በሚሆኑበት ወቅት በሚከፍሉት አነስተኛ መዋጮ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት ከመድህን ቋቱ ወጪ በሚደረግ ገንዘብ የጤና ወጪአቸው ይሸፈንላቸዋል፡፡