የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የመገናኘ ብዙሀን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠየቀ

    ጋዜጣዊ መግለጫ(Press release)

የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ ቅድሜ የካቲት 9 በተቋሙ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው ህብረተሰቡ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሀን ህብረተሰቡ አገልግሎቱ ያለውን ጠቀሜታ እንዲረዳ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራውን በስፋት በመስራት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቋል ፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው ኤጀንሲው ሁልጊዜ በየአመቱ ከታህሳስ እስከ የካቲት ያሉትን ሶስት ወራት የአዲስ አባላት መመዝገቢያና የነባር አባላት ደግሞ የአባልነት ማደሻ ጊዜ አድረጎ እየሰራ ቢግኝም በህበረተሰቡ ዘንድ ስለ አገልግሎቱ ያለው ግንዛቤ በቂ ባለመሆኑ የአባላት ቁጥር እንደተፈለገው አጥጋቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡  ስለዚህም የያዝነውን የየካቲት ወር የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ወር አድርጐ በመሰየም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መደበኛ ባልሆነ ገቢ የሚተዳደሩትን ወይንም ደሞዝተኛ ያልሆኑ በገጠርና በከተማ የሚገኙ ዜጎችን የሚያቅፍ የመድህን ሥርዓት ሲሆን በሀገራችን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ክልሎች ማለትም በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባሉ 13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ በአሁኑ ሰዓት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 522 ወረዳዎች ማስፋፋት ተችሏል፡፡ከነዘህ ውስጥ በ416 ወረዳዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል በአሁኑ ሰዓትም ፕሮግራሙ እስካሁን ባልተጀመረባቸው እንደ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ለማስጀመር እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኘ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተገልጾል፡፡

የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ ሁለት የጤና መድህን ሥርዓት ዓይነቶች ትግበራና አፈጻጸምን ለመምራት፣ ለማስተባበርና ለመከታተል በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተቋቋመ ተቋም ሲሆን ዋና ዓላማውም የጤና መድህን ሥርዓትን በአገራችን ተግባራዊ በማድረግ የጤና ወጪ በህብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለውን ጫና በመቀነስ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እና የጤና አጠቃቀምን ማጎልበት ነው፡፡  በዚህም መሠረት የማህበራዊ ጤና መድህን መደበኛ በሆነው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማራውን የህብረተሰብ ተጠቃሚ እንደሚደርግ ታምኖበት የቅድመ ዝግጅት ሥራው ተጠናቆ መንግስት ሲወስን ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፡፡ በሌላ በኩል የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም መደበኛ ባልሆነው  ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማራውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እያደረገ ያለ ስርአት ነው፡፡

Source: 
Ethiopian Health Insurance Agency