በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ከ22.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ታቅፈዋል
በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ከ22.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ታቅፈዋል
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት (ማዐጤመ) በከተማና በገጠር መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ የጤና መድህን ዓይነት በ2003 ዓ.ም በ13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ በትግራይ፣ በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ብ/ብ/ህዝቦች ክልሎች ተጀምሮ ከሙከራ ወረዳዎች የተገኘውን ልምድ በመቀመር ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛን ኪሮስ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በ2011 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እንቅስቃሴ በ5 ክልሎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር በሚገኙ 657 ወረዳዎች ተጀምሮ 509 ወረዳዎች ቅድመ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ለአባላቶቻቻውና ቤተሰቦቻቸው የህክምና አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ በነዚህ ወረዳዎች የሚኖሩ ከ22.5 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎችም በጤና መድህን ስርዓቱ ታቅፈዋል፡፡
በጤና መድህን ስርዓቱ ከታቀፉት ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና አመታዊ የጤና መድህን መዋጯቸውን መክፈል የማይችሉ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጤና መድህን መዋጯቸው በመንግስት እንዲሸፈንላቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአባላት መዋጮ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመው፣ የጤና መድህን አባላትና ቤተሰቦቻቸው በጤና መድህኑ ላገኙት የህክምና አገልግሎት ከ 617 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈፀሙንም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛን ኪሮስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የ2012 የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት የአባልነት ምዝገባና ዕድሳት መርሃግብር ከታህሳስ ወር ጀምሮ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የጤና መድህን አባል የሆኑ ሰዎችን የአባልነት ዕድሳት እንዲሁም አዳዲስ አባላትን ወደ ጤና መድህኑ የማስገባት ስራ በየክልሎቹ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የአባልነት ምዝገባና የዕድሳት ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊትም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተግባራዊ በተደረገባቸው ክልሎች የሚገኙ ዜጎች ለጤና መድህን አባልነት የሚጠበቀውን ዓመታዊ መዋጮ በመክፈል እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበው፣ የጤና መድህን አባል የሆኑ ዜጎችም አባልነታቸውን በማደስ እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ለማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ትግበራ ስኬት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ክልሎች፣ የጤና ሴክተር ባለድርሻ አካላት፣ ዞኖችና ወረዳዎች ነዋሪዎቻቸውን በጤና መድህን ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመሩትን የንቅናቄ ዘመቻ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ለሀገራችን አዲስ እንደመሆኑ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ለህብረተሰቡ ስለጤና መድህን ጠቀሜታ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ዘገባዎችን በማቅረብ ለጤና መድህን ስርዓቱ ስኬት ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት በገጠርና በከተሞች አካባቢ መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣ በእርስ በርስ የመደጋገፍ መርህ መሰረት በተናጠል ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ የጤና ወጪ ጫና በማስቀረት ቤተሰቦች ወደ ከፋ ድህነት እንዳይገቡ የሚታደግ ስርዓት ነው፡፡