በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ከ32 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ታቅፈዋል
በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ከ32 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ታቅፈዋል
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት (ማዐጤመ) በከተማና በገጠር መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ የጤና መድህን ዓይነት በ2003 ዓ.ም በ13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ብ/ብ/ህዝቦች ክልሎች ተጀምሮ ከሙከራ ወረዳዎች የተገኘውን ልምድ በመቀመር ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አለሙ አኖ እንዳስታወቁት፣ በ2012 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እንቅስቃሴ በሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በሚገኙ 827 ወረዳዎች ተጀምሮ 743 ወረዳዎች ቅድመ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ለአባላቶቻቻውና ቤተሰቦቻቸው የህክምና አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ በነዚህ ወረዳዎች የሚኖሩ ከ32 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች በጤና መድህን ስርዓቱ ታቅፈዋል፡፡
በጤና መድህን ስርዓቱ ከታቀፉት ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና አመታዊ የጤና መድህን መዋጯቸውን መክፈል የማይችሉ ከ6.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጤና መድህን መዋጯቸው በመንግስት እንዲሸፈንላቸው ተደርጓልም ብለዋል፡፡
በ2012 በጀት ዓመት ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአባላት መዋጮ እና ከድጎማ በጀት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመው፣ የጤና መድህን አባላትና ቤተሰቦቻቸው በጤና መድህኑ ላገኙት የህክምና አገልግሎት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ 524 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈፀሙንም የኤጀንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አለሙ አኖ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት በገጠርና በከተሞች አካባቢ መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣ በእርስ በርስ የመደጋገፍ መርህ መሰረት በተናጠል ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ የጤና ወጪ ጫና በማስቀረት ቤተሰቦች ወደ ከፋ ድህነት እንዳይገቡ የሚታደግ ስርዓት ነው፡፡