የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ አመራሮች እና ባለሙያዎች በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት የጨንቻ ወረዳን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ፡፡

በኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለሙ አኖ የተመራው ቡድን ባደረገው የመስክ ጉብኝት የወረዳው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ትግበራ አበረታች መሆኑን ተመልክቷል፡፡

በጨንቻ ወረዳ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተቋም ከጤና መድህን አባላት የተሰበሰበ ገንዘብ በሙሉ ወደ ባንክ ገቢ መደረጉ፣ የተሰራጩ ደረሰኞች ሙሉ ለሙሉ ተመላሽ መደረጋቸው፣ የአባላት መረጃ በአግባቡ መያዙ፣ የመታወቂያ ስርጭት ከ99 በመቶ በላይ መሆኑ፣ እንዲሁም ለአባላት የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተከናወነው ተግባር ለሌሎች ወረዳዎች ተሞክሮ እንደሚሆን አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡

በወረዳው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል መሆን ከሚገባቸው አባወራ/እማወራዎች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት የጤና መድህን አባል ሆነዋል፡፡ አባል ከሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ በመጀመሪያው ሩብ አመት ብቻ 2 ሺህ 448 ሰዎች ላገኙት ህክምና 262 ሺህ 362 ብር ክፍያ ተፈጽሟል ፡፡

በጨንቻ ወረዳ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተቋም ከሚያዝያ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለጤና መድህን አባላትና ቤተሰቦቻቸው የህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ያታወቃል፡፡

Source: 
Ethiopian Health Insurance Agency