ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመላ ሀገሪቱ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ፡፡
ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመላ ሀገሪቱ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ የ2011 የዝግጅት ምእራፍ አፈጻጸም ግምገማ መርሀ ግብር ከጥቅምት 5 እሰከ 7 በቢሸፍቱ ከተማ ባካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው እሰከ 2010 በጀት አመት ማጠቃለያ ድረስ በመላ ሀገሪቱ ከ 20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረግ መቻሉ ተገልጾል፡፡
በዚህ የዝግጅት ምእራፍ አፈጻጸም ግምገማ መርሀ ግብር ላይ የዳይሬክተሮችና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የዝግጅት ምእራፍ ሪፖርት እና የቀጣይ ሁለተኛ ሩብ አመት እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደረጎበታል፡፡ በውይይቱ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች ከተሳታፊዎቹ የተነሱ ሲሆን በተለይም ለስራ እንቅፋት እየሆነ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የህግ ውክልና ጉዳይ ከተነሱት ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎች ናቸው፡፡
በውይይቱ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ አብርሃ እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አለሙ አኖ ከተሳታፊዎቹ በተነሱ ሀሳቦች ላይ በሰጡት ማብራሪያ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስራዉ ከክልሎች ጋራ በጋራ ቢሰራም በዋናነት የስራዉ ባለቤት ግን ኤጀንሲው እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ በተነሳው ችግር በሰጡት አስተያየት የመልካም አስተዳደር ችግር በየደረጃው በተቀመጠ አሰራር መፈታት እንዳለበት አቅጣጫ አሰቀምጠዋል፡፡ በተለይም የተለያዩ አደረጃጀቶችና በየደረጃው ያሉ መድረኮችን መጠቀም አሰፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከዝግጅት ምእራፍ አፈጻጸም ግምገማ ቀጥሎ የ2011 በጀት አመት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የምዝገባና እድሳት ስራዎች የሶስት ወራት የንቅናቄ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በሰነዱ ላይ የዝግጅት ምእራፍ እና የትግበራ ምእራፍ በዝርዝር የተቀመጡ ሲሆን እነዚህ ስራዎች በታለመላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ተጠይቋል፡፡
የማህበረስ አቀፍ የጤና መድህን የ2011 በጀት አመት የአዲስ አባላት ምዝገባና ነባር አባላት እድሳ ከታህሳስ እስከ የካቲት ለማከናወን የታቀደ ሲሆን በዚህ ወቅት የሚኖረውን የስራ እንቅስቃሴ በተደራጀ መልኩ ለመምራት ሰነዱ አቅጣጫ አሰቀምጧል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ለመተግበር እንቅስቃሴ በተጀመረባቸዉ 522 ወረዳዎች አሰከ 2010 በጀት አመት ማጠናቀቂያ ድረስ በ340 ወረዳዎች ማድረስ የተቻለ ሲሆን በዚህ በጀት አመት ሽፋኑን ከ522 ወደ 643 ማድረስ ሲሆን የአባላት ሽፋኑን ደግሞ ከ47% ወደ 75% ፐርስንት ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል፡፡