በድሬደዋ፣ በሀረሪ እና በሱማሌ ክልል ለሚገኙ የሚድያ አካላት ስልጠና ተሰጠ::

የጤና መድህን ጽንሰ ሀሳብና የሀገራት ተሞክሮ ፣ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በኢትዮጵያ ያለበት ደረጃ እና ጤና መድህንን በሀገራችን ተደራሽ ለማድረግ ከሚድያ አካላት ምን ይጠበቃል በሚሉ ርእሶች ዙሪያ በድሬደዋ፣ በሀረሪ እና በሱማሌ ክልል ለሚገኙ የሚድያ አካላት ለሁለት ቀናት የቆየ ስልጠና በሀረር ከተማ ተሰጠ፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ በመገኘት ለሰልጣኞቹ መልዕክት ያስተላለፉት የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም እንዳስገነዘቡት የዚህ ስልጠና ለሚድያ አካላት መዘጋጀቱ በቅርብ በክልላችን ለማስጀመር ላሰብነው ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መደህን አግልግሎት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከመስጠት አንጻር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ይህን ስልጠና ከኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ ኮሚኒኬሽንና ሞቢላይዜሽን ዳይሬክቶሬት ጋር በመሆን ያዘጋጁት በኤጀንሲው የድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኬያጅ አቶ ጉደታ አበበ ይህን ስልጠና መስጠት ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልጹ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በሀገራችን በርካታ አካባቢዎች ተጀምሮ በጥሩ አፈጻጸም ላይ ቢገኝም ጋምቤላን ጨምሮ በድሬዳዋ፣ በሀረሪ እና በጂግጂጋ ግን በተለያየ ምክንያት እሰካሁን ሳይጀመር ቆይቷል። ፕሮግራሙን በነዚህ ቦታዎች ለማስጀመር የፕሮግራሙን ጠቀሜታ ለህብረተሰቡና ለአመራሩ ለማሰገንዘብ ሲባል ለሚድያ አካላቱ ስልጠናው ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ስልጣኞች እያንዳንዳቸው ከኪሳቸው 260 ብር በማዋጣት ለ 53 ሰዎች የአንድ አመት የጤና ዋስትና ለመግዛት የሚያስችል ብር 13780 ሺ ብር ገቢ በማድረግ አርአያነት ያለው ስራ ሰርተዋል።

በዚህ አመት ተመሳሳይ ስልጠና በፌደራል በኦሮሚያ በደቡብ እና በአማራ ክልል የተሰጠ ሲሆን በዚህም ሚድያዎችን በመጠቀም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንን አስመልክቶ የህብረተሰቡን ግንዛቤን ማስፋት ተችሏል።

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከተማና በገጠር መደበኛ ባልሆነ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመድህን አይነት ሲሆን በአሁን ሰአት 22. 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በዚህ ስር ታቅፈው አገልግሎት እያገኙ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

Source: 
Ethiopian Health Insurance Agency