የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግስት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ክልላዊ ኮንፈረንስ በአርባምንጭ ከተማ ተካሄደ

በክልላዊ ኮንፈረንሱ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን እና የልዩ ወረዳ አመራሮች ተሳትፈውበታል፡፡

የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ በክልላዊ ኮንፈረንሱ ላይ እንደተናገሩት፣ በ2003 ዓ.ም በ13 ወረዳዎች የተጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገራዊ ትግበራ በአሁኑ ወቅት 770 ወረዳዎች ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከ32 ሚሊዮን በላይ ዜጎችም በጤና መድህኑ ታቅፈዋል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ለዜጎቻችን የጤና አገልግሎትን በፍትሀዊነት ለማድረስ የሚያግዝ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ህብረተሰቡን በማነቃነቅ ለፕሮግራሙ መሳካት የመሪነት ሚናውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሐይለማርያም ተስፋዬ ክልላዊ ኮንፈረንሱን ሲከፍቱ እንዳሉት፣ የዜጎች ጤና ባልተጠበቀበት ሁኔታ የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ ሁሉም አባወራ/እማወራዎች በጤና መድህኑ እንዲታቀፉ አመራሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል፡፡

በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግስት 130 ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተግብረው ለጤና መድህን አባሎቻቸው የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች 21 ወረዳዎች ደግሞ ፕሮግራሙን ለመጀመር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

Source: 
Ethiopian Health Insurance Agency